1ኛ የዮሐንስ መልእክት
፩ ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ፪ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ ፫ እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። ፬ ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን። ፭ ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት። ፮ ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤ ፯ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። ፰ ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። ፱ በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ፲ ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።