፬
 ፩ እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን።  ፪ እንደዚህም ሲሆን፥ በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል።  ፫ ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤  ፬ በራሴ ላይ ምንም አላውቅምና፥ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ እኔን የሚፈርድ ግን ጌታ ነው።  ፭ ስለዚህም በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል።  ፮ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ። ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ።  ፯ አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?  ፰ አሁን ጠግባችኋል፤ አሁንስ ባለ ጠጎች ሆናችኋል፤ ያለ እኛ ነግሣችኋል፤ እኛ ደግሞ ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ መልካም ይሆን ነበር።  ፱ ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልና፤ እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛልና።  ፲ እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን እናንተ ግን ኃይለኞች ናችሁ፤ እናንተ የከበራችሁ ናችሁ እኛ ግን የተዋረድን ነን።  ፲፩ እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥  ፲፪ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤  ፲፫ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል።  ፲፬ እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም።  ፲፭ በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና።  ፲፮ እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ።  ፲፯ ስለዚህ የምወደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፥ እኔም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደማስተምር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚሆነውን መንገዴን እርሱ ያሳስባችኋል።  ፲፰ አንዳንዱ ግን ወደ እናንተ የማልመጣ እየመሰላቸው የታበዩ አሉ፤  ፲፱ ነገር ግን ጌታ ቢፈቅድ ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፥ የትዕቢተኞችንም ኃይል አውቃለሁ እንጂ ቃላቸውን አይደለም፤  ፳ የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና።  ፳፩ ምን ትወዳላችሁ? በበትር ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ ልምጣባችሁን?