፲፪
 ፩ ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ።  ፪ አሕዛብ ሳላችሁ በማናቸውም ጊዜ እንደምትመሩ ድምፅ ወደሌላቸው ወደ ጣዖታት እንደ ተወሰዳችሁ ታውቃላችሁ።  ፫ ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር። ኢየሱስ የተረገመ ነው የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር። ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ።  ፬ የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤  ፭ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤  ፮ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።  ፯ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል።  ፰ ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥  ፱ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥  ፲ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤  ፲፩ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።  ፲፪ አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤  ፲፫ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።  ፲፬ አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና።  ፲፭ እግር። እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፥ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን?  ፲፮ ጆሮም። እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን?  ፲፯ አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ?  ፲፰ አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል።  ፲፱ ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ?  ፳ ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው።  ፳፩ ዓይን እጅን። አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን። አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም።  ፳፪ ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤  ፳፫ ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤  ፳፬-፳፮ አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።  ፳፯ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።  ፳፰ እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።  ፳፱ ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን?  ፴ ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን?  ፴፩ ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ።