፪
 ፩ ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤  ፪ እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው።  ፫ ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤  ፬ ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ።  ፭ የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም።  ፮ አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥  ፯ ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤  ፰ ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና።  ፱ ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤  ፲ ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ።  ፲፩ ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና።  ፲፪ አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ።  ፲፫ የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ።  ፲፬ ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን። አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት።  ፲፭ እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤  ፲፮ ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።  ፲፯ ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም።  ፲፰ ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና።  ፲፱ እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና።  ፳ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።  ፳፩ የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።