፬
 ፩ ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥  ፪ ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው።  ፫ እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤  ፬ ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤  ፭ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ።  ፮ ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።  ፯ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።  ፰ ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤  ፱ አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን?  ፲ ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ።  ፲፩ ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ።  ፲፪ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና። እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። አንዳችም አልበደላችሁኝም።  ፲፫ በመጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ፥  ፲፬ በሥጋዬም ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትምና አልተጸየፋችሁትም ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ።  ፲፭ እንግዲህ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ።  ፲፮ እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን?  ፲፯ በብርቱ ይፈልጉአችኋል፥ ለመልካም አይደለም ነገር ግን በብርቱ ትፈልጉአቸው ዘንድ በውጭ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ።  ፲፰ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው።  ፲፱ ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል።  ፳ ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ።  ፳፩ እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ።  ፳፪ አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና።  ፳፫ ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል።  ፳፬ ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት።  ፳፭ ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና።  ፳፮ ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት።  ፳፯ አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል።  ፳፰ እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን።  ፳፱ ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው።  ፴ ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት።  ፴፩ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም።