የማርቆስ ወንጌል  
 ፩
 ፩ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።  ፪-፬ ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ።  ፭ የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።  ፮ ዮሐንስም የግመል ጠጉር ለብሶ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር።  ፯ ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።  ፰ እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።  ፱ በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ።  ፲ ወዲያውም ከውኃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና። የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥  ፲፩ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ።  ፲፪ ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ አወጣው።  ፲፫ በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ ከአራዊትም ጋር ነበረ፥ መላእክቱም አገለገሉት።  ፲፬-፲፮ በገሊላ ባሕርም አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና።  ፲፯ ኢየሱስም። በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው።  ፲፰ ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።  ፲፱ ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ደግሞ በታንኳ ላይ መረባቸውን ሲያበጁ አየ።  ፳ ወዲያውም ጠራቸው አባታቸውንም ዘብዴዎስን ከሞያተኞቹ ጋር በታንኳ ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ።  ፳፩ ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ።  ፳፪ እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ።  ፳፫ በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤  ፳፬ እርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።  ፳፭ ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው።  ፳፮ ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ።  ፳፯ ሁሉም። ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ።  ፳፰ ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ።  ፳፱ ወዲያውም ከምኵራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገባ።  ፴ የስምዖንም አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፥ ስለ እርስዋም ወዲያው ነገሩት።  ፴፩ ቀርቦም እጅዋን ይዞ አስነሣት ንዳዱም ወዲያው ለቀቃትና አገለገለቻቸው።  ፴፪ ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤  ፴፫ ከተማይቱም ሁላ በደጅ ተሰብስባ ነበር።  ፴፬ በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፥ ብዙዎችንም አጋንንት አወጣ፥ አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም።  ፴፭ ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ።  ፴፮ ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩትም ገሥግሠው ተከተሉት፥  ፴፯ ባገኙትም ጊዜ። ሁሉ ይፈልጉሃል አሉት።  ፴፰ እርሱም። በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደ ሌላ ስፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ ስለዚህ ወጥቻለሁና አላቸው።  ፴፱ በምኵራባቸውም እየሰበከ አጋንንትንም እያወጣ ወደ ገሊላ ሁሉ መጣ።  ፵ ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ ተንበረከከና። ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው።  ፵፩ ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው።  ፵፪ በተናገረም ጊዜ ለምጹ ወዲያው ለቀቀውና ነጻ።  ፵፫ በብርቱም ተናግሮ ወዲያው አወጣው፤  ፵፬ ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ አለው።  ፵፭ እርሱ ግን ሲወጣ ብዙ ሊሰብክና ነገሩን ሊያወራ ጀመረ፥ ስለዚህም ኢየሱስ ተገልጦ ወደ ከተማ መግባት ወደ ፊት ተሳነው፥ ነገር ግን በውጭ በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ከየስፍራውም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።