የይሁዳ መልእክት  
 ፩
 ፩ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤  ፪ ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ።  ፫ ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።  ፬ ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።  ፭ ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ።  ፮ መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።  ፯ እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።  ፰ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ።  ፱ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር። ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።  ፲ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ።  ፲፩ ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።  ፲፪ እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥  ፲፫ የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው።  ፲፬-፲፮ እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል።  ፲፯ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤  ፲፰ እነርሱ። በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና።  ፲፱ እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው።  ፳ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥  ፳፩ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።  ፳፪ አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥  ፳፫ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።  ፳፬ ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው  ፳፭ ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።