፬
 ፩ በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?  ፪ ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤  ፫ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።  ፬ አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።  ፭ ወይስ መጽሐፍ። በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን?  ፮ ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ። እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል።  ፯ እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤  ፰ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።  ፱ ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ።  ፲ በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።  ፲፩ ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም።  ፲፪ ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?  ፲፫ አሁንም። ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና።  ፲፬ ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና።  ፲፭ በዚህ ፈንታ። ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል።  ፲፮ አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።  ፲፯ እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።