፪
 ፩ እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም።  ፪ በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና።  ፫ እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤  ፬-፮ በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤  ፯ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።  ፰ ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤  ፱ ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።  ፲ መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው።  ፲፩ በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም።  ፲፪ እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።  ፲፫ መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።  ፲፬ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።  ፲፭ መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።  ፲፮ እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።