፪
 ፩ እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥  ፪-፬ በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ፥  ፭ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።  ፮ በመጽሐፍ። እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና።  ፯ እንግዲህ ክብሩ ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ፤  ፰ የማያምኑ ስለ ሆኑ በቃሉ ይሰናከሉበታልና፤ ለዚህ ደግሞ የተመደቡ ናቸው።  ፱ እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤  ፲ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።  ፲፩ ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤  ፲፪ ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፥ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፥ በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።  ፲፫ ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤  ፲፬ ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ።  ፲፭ በጎ እያደረጋችሁ፥ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፤  ፲፮ አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ።  ፲፯ ሁሉን አክብሩ፥ ወንድሞችን ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ንጉሥን አክብሩ።  ፲፰ ሎሌዎች ሆይ፥ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ።  ፲፱ በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና።  ፳ ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል።  ፳፩ የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።  ፳፪ እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤  ፳፫ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤  ፳፬ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤*ፍ1*  ፳፭ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።