2ኛ የዮሐንስ መልእክት  
 ፩
 ፩-፫ ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ።  ፬ ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል።  ፭ አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም።  ፮ እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት።  ፯ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው።  ፰ ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።  ፱ ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።  ፲ ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤  ፲፩ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።  ፲፪ እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፥ ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።  ፲፫ የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።