2ኛ የጴጥሮስ መልእክት  
 ፩
 ፩ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤  ፪-፬ ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።  ፭ ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥  ፮ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥  ፯ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።  ፰ እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤  ፱ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል።  ፲ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና።  ፲፩ እንዲሁ ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና።  ፲፪ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ምንም ብትጸኑ፥ ስለ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም።  ፲፫ ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል።  ፲፬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና።  ፲፭ ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ።  ፲፮ የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።  ፲፯ ከገናናው ክብር። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤  ፲፰ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።  ፲፱ ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።  ፳ ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤  ፳፩ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።