፰
 ፩ ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።  ፪ እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ እያለ ሰገደለት።  ፫ እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ።  ፬ ኢየሱስም። ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ አለው።  ፭ ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥  ፮ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል ብሎ ለመነው።  ፯ ኢየሱስም። እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው።  ፰ የመቶ አለቃውም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል።  ፱ እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም። ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም። ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም። ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው።  ፲ ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።  ፲፩ እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤  ፲፪ የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።  ፲፫ ኢየሱስም ለመቶ አለቃ። ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ።  ፲፬ ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤  ፲፭ እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው።  ፲፮-፲፰ ኢየሱስም ብዙ ሰዎች ሲከቡት አይቶ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ።  ፲፱ አንድ ጻፊም ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው።  ፳ ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው።  ፳፩ ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው።  ፳፪ ኢየሱስም። ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው።  ፳፫ ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት።  ፳፬ እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር።  ፳፭ ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት።  ፳፮ እርሱም። እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ።  ፳፯ ሰዎቹም። ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ።  ፳፰ ወደ ማዶም ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተገናኙት፤ እነርሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስኪሳነው ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ።  ፳፱ እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ።  ፴ ከእነርሱም ርቆ የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማራ ነበር።  ፴፩ አጋንንቱም። ታወጣንስ እንደሆንህ፥ ወደ እሪያው መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት። ሂዱ አላቸው።  ፴፪ እነርሱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ሄዱና ገቡ፤ እነሆም፥ የእሪያዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባሕር እየተጣደፉ ሮጡ በውኃም ውስጥ ሞቱ።  ፴፫ እረኞችም ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ሄደው ነገሩን ሁሉ አጋንንትም በአደሩባቸው የሆነውን አወሩ።  ፴፬ እነሆም፥ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ፥ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት።