፲፰
 ፩ በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው። በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? አሉት።  ፪ ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ  ፫ እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።  ፬ እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው።  ፭ እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤  ፮ በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር።  ፯ ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት።  ፰ እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ህይወት መግባት ይሻልሀል።  ፱ ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።  ፲ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና።  ፲፩ የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና።  ፲፪ ምን ይመስላችኋል? ለአንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢባዝን፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ሄዶም የባዘነውን አይፈልግምን?  ፲፫ ቢያገኘውም፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልባዘኑቱ ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል።  ፲፬ እንደዚሁ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም።  ፲፭ ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤  ፲፮ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤  ፲፯ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።  ፲፰ እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።  ፲፱ ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል።  ፳ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።  ፳፩ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው።  ፳፪ ኢየሱስ እንዲህ አለው። እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም።  ፳፫ ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች።  ፳፬ መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ።  ፳፭ የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ።  ፳፮ ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና። ጌታ ሆይ፥ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው።  ፳፯ የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት።  ፳፰ ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና። ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው።  ፳፱ ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ። ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ ብሎ ለመነው።  ፴ እርሱም አልወደደም፥ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው።  ፴፩ ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፥ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ።  ፴፪ ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ። አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤  ፴፫ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው።  ፴፬ ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው።  ፴፭ ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።