፪
 ፩ ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ደግሞ ገብቶ በቤት እንደ ሆነ ተሰማ።  ፪ በደጅ ያለው ስፍራም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ይነግራቸው ነበር።  ፫ አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት።  ፬ ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፥ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ።  ፭ ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው።  ፮ ከጻፎችም አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም። ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል?  ፯ ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው አሰቡ።  ፰ ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ እንዲህ አላቸው። በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ?  ፱ ሽባውን። ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?  ፲ ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤  ፲፩ ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው።  ፲፪ ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፥ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ተገረሙና። እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም ብለው እግዚአብሔርን አከበሩ።  ፲፫ ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው።  ፲፬ ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው።  ፲፭ በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ ይከተሉትም ነበር።  ፲፮ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ። ከቀራ ጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው? አሉ።  ፲፯ ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።  ፲፰ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጦሙ ነበር። መጥተውም። የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጦሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት።  ፲፱ ኢየሱስም አላቸው። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጦሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም።  ፳ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ።  ፳፩ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል።  ፳፪ በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ።  ፳፫ በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር።  ፳፬ ፈሪሳውያንም። እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ? አሉት።  ፳፭ እርሱም። ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ አብያተር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥  ፳፮ ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው።  ፳፯ ደግሞ። ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤  ፳፰ እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።