፳፩
 ፩ ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ።  ፪ አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና።  ፫ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤  ፬ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ።  ፭ አንዳንዶቹም ስለ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ። ይህማ የምታዩት ሁሉ፥  ፮ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል አለ።  ፯ እነርሱም። መምህር ሆይ፥ እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት።  ፰ እንዲህም አለ። እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች። እኔ ነኝ፥ ዘመኑም ቀርቦአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ።  ፱ ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም።  ፲ በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤  ፲፩ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል።  ፲፪ ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤  ፲፫ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል።  ፲፬ ሰለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤  ፲፭ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።  ፲፮ ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤  ፲፯ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።  ፲፰ ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤  ፲፱ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።  ፳ ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።  ፳፩ የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፥ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ፤  ፳፪ የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል ጊዜ ነውና።  ፳፫ በዚያን ወራት ለእርጕዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይሆናልና፤  ፳፬ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።  ፳፭ በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤  ፳፮ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና።  ፳፯ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።  ፳፰ ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።  ፳፱ ምሳሌንም ነገራቸው እንዲህ ሲል። በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤  ፴ ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።  ፴፩ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ።  ፴፪ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።  ፴፫ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።  ፴፬ ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤  ፴፭ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።  ፴፮ እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።  ፴፯ ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፥ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር።  ፴፰ ሕዝቡም ሁሉ ይሰሙት ዘንድ ማልደው በመቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።