፳
 ፩ መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ አትክልት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ሰውን ትመስላለችና።  ፪ ሠራተኞችንም በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ሰደዳቸው።  ፫ በሦስት ሰዓትም ወጥቶ ሥራ የፈቱ ሌሎችን በአደባባይ ቆመው አየ፥  ፬ እነዚያንም። እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ አላቸው። እነርሱም ሄዱ።  ፭ ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ።  ፮ በአሥራ አንደኛውም ሰዓት ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና። ሥራ ፈትታችሁ ቀኑን ሁሉ በዚህ ስለ ምን ትቆማላችሁ? አላቸው።  ፯ የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው አሉት። እርሱም። እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም ትቀበላላችሁ አላቸው።  ፰ በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን። ሠራተኞችን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው አለው።  ፱ በአሥራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ።  ፲ ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ።  ፲፩-፲፫ እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው። ወዳጄ ሆይ፥ አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን?  ፲፬ ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን?  ፲፭ ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን?  ፲፮ እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።  ፲፯ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ሳለ፥ በመንገድ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ብቻቸውን ወደ እርሱ አቅርቦ።  ፲፰ እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥  ፲፱ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው።  ፳ በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆችዋ ጋር እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ወደ እርሱ ቀረበች።  ፳፩ እርሱም። ምን ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም። እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ አለችው።  ፳፪ ኢየሱስ ግን መልሶ። የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አለ። እንችላለን አሉት።  ፳፫ እርሱም። ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለሁም አላቸው።  ፳፬ አሥሩም ሰምተው በሁለቱ ወንድማማች ተቈጡ።  ፳፭ ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ።  ፳፮ በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥  ፳፯ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤  ፳፰ እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።  ፳፱ ከኢያሪኮም ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።  ፴ እነሆም፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንዲያልፍ በሰሙ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን ብለው ጮኹ።  ፴፩ ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን እያሉ አብዝተው ጮኹ።  ፴፪ ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አለ።  ፴፫ ጌታ ሆይ፥ ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ አሉት።  ፴፬ ኢየሱስም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፥ ወዲያውም አዩና ተከተሉት።