የዮሐንስ ወንጌል  
 ፩
 ፩ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።  ፪ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።  ፫ ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።  ፬ በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።  ፭ ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።  ፮ ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤  ፯ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።  ፰ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።  ፱ ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።  ፲ በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።  ፲፩ የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።  ፲፪ ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤  ፲፫ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።  ፲፬ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።  ፲፭ ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።  ፲፮ እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤  ፲፯ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።  ፲፰ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።  ፲፱ አይሁድም። አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው።  ፳ መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ።  ፳፩ እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ።  ፳፪ እንኪያስ። ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት።  ፳፫ እርሱም። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ።  ፳፬-፳፮ ዮሐንስ መልሶ። እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤  ፳፯ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው።  ፳፰ ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ።  ፳፱ በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።  ፴ አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።  ፴፩ እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ።  ፴፪ ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ።  ፴፫ እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ። መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።  ፴፬ እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።  ፴፭ በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥  ፴፮ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ።  ፴፯ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።  ፴፰-፵ መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ።  ፵፩ ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ።  ፵፪ እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና። መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው።  ፵፫ ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ። አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው።  ፵፬ በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና። ተከተለኝ አለው።  ፵፭ ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ።  ፵፮ ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ። ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው።  ፵፯ ናትናኤልም። ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ። መጥተህ እይ አለው።  ፵፰ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ። ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ።  ፵፱ ናትናኤልም። ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ። ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው።  ፶ ናትናኤልም መልሶ። መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው።  ፶፩ ኢየሱስም መልሶ። ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው።  ፶፪ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው።