፭
 ፩ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤  ፪ የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና።  ፫ ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።  ፬ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥  ፭ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤  ፮ እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ።  ፯ የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፥ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤  ፰ እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር፤  ፱ እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ።  ፲ የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ።  ፲፩ ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው።  ፲፪-፲፬ ወንድሞች ሆይ፥ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ።  ፲፭ ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።  ፲፮ ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤  ፲፯-፲፱ መንፈስን አታጥፉ፤  ፳-፳፪ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ።  ፳፫ የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።  ፳፬ የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል።  ፳፭ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኛ ጸልዩ።  ፳፮ ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ።  ፳፯ ይህ መልእክት ለቅዱሳን ወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አምላችኋለሁ።  ፳፰ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።