፲፮
 ፩ በክንክራኦስ ባለች ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የምትሆን እኅታችንን ፌቤንን አደራ ብያችኋለሁ፤  ፪ ለቅዱሳን እንደሚገባ በጌታ ተቀበሉአት፥ እርስዋ ለብዙዎች ለእኔም ለራሴ ደጋፊ ነበረችና፥ ከእናንተም በምትፈልገው በማናቸውም ነገር እርዱአት።  ፫ በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤  ፬ እነርሱም ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት አቀረቡ፥ የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም፤  ፭ በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእስያ ለክርስቶስ በኵራት ለሆነው ለምወደው ለአጤኔጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፮ ስለ እናንተ ብዙ ለደከመች ለማርያ ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፯ በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ፥ ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ፥ አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንዲራኒቆንና ለዩልያን ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፰ በጌታ ለምወደው ለጵልያጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፱ በክርስቶስ አብሮን ለሚሠራ ለኢሩባኖን ለምወደውም ለስንጣክን ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፲ በክርስቶስ መሆኑ ተፈትኖ ለተመሰገነው ለኤጤሌን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከአርስጣባሉ ቤተ ሰዎች ላሉት ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፲፩ ለዘመዴ ለሄሮድዮና ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከንርቀሱ ቤተ ሰዎች በጌታ ላሉት ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፲፪ በጌታ ሆነው ለሚደክሙ ለፕሮፊሞናና ለጢሮፊሞሳ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጌታ እጅግ ለደከመች ለተወደደች ለጠርሲዳ ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፲፫ በጌታ ሆኖ ለታወቀ ለሩፎን ለእኔና ለእርሱም እናት ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፲፬ ለአስቀሪጦንና ለአፍለሶንጳ ለሄሮሜንም ለጳጥሮባም ለሄርማንም ከእነርሱም ጋር ላሉ ወንድሞች ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፲፭ ለፍሌጎንና ለዩልያ ለኔርያና ለእኅቱም ለአልንጦንም ከእነርሱ ጋር ላሉ ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ።  ፲፮ በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።  ፲፯ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤  ፲፰ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ።  ፲፱ መታዘዛችሁ ለሁሉ ተወርቶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለበጎ ነገር ጥበበኞች ለክፉም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ።  ፳ የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።  ፳፩ አብሮኝ የሚሠራ ጢሞቴዎስ ዘመዶቼም ሉቂዮስና ኢያሶን ሱሲጴጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።  ፳፪ ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ።  ፳፫ የእኔና የቤተ ክርስቲያን ሁሉ አስተናጋጅ ጋይዮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። የከተማው መጋቢ ኤርስጦስ ወንድማችንም ቁአስጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።  ፳፬ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።  ፳፭-፳፯ ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።