እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን? የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ። ፫-፭እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም፥ እኅት ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን? ወይስ ሥራን ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን? ከቶ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይስ ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማን ነው? ይህን በሰው ሥልጣን ብቻ እላለሁን? ሕግስ ደግሞ ያን አይልምን? የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ተብሎ በሙሴ ሕግ ተጽፎአልና። እግዚአብሔርስ ስለ በሬዎች ይገደዋልን? ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን? የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው በእውነት ስለ እኛ ተጽፎአል። ፲፩እኛ መንፈሳዊን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር እኛ ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? ፲፪ሌሎች በእናንተ ላይ ይህን መብት የሚካፈሉ ከሆኑ እኛማ ይልቁን እንዴታ? ነገር ግን የክርስቶስን ወንጌል እንዳንከለክል በሁሉ እንታገሣለን እንጂ በዚህ መብት አልተጠቀምንም። ፲፫በመቅደስ ነገር የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሆነውን ነገርን እንዲመገቡ፥ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን? ፲፬እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። ፲፭እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። ፲፮ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ። ፲፯ይህን በፈቃዴ ባደርገው ደመወዝ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል። ፲፰እንግዲህ ደመወዜ ምንድር ነው? ወንጌልን እየሰበክሁ በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ እንዳልጠቀም ወንጌልን ያለ ዋጋ ብናገር ነው። ፲፱ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ ፳፩ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ህግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ ፳፪ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። ፳፫በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። ፳፬በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። ፳፭የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። ፳፮ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ፳፯ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።