፩ወንድሞች ሆይ፥ ራሳችሁ ወደ እናንተ መግባታችን ከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና። ፪ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን። ፫ልመናችን ከስሕተት ወይም ከርኵሰት ወይም ከተንኰል አልነበረምና፤ ፬ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም። ፭እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም፤ ፮የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም። ፯ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ ፰እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና። ፱ወንድሞች ሆይ፥ ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋልና፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን። ፲በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ ፲፩-፲፫ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። ፲፬እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና። ፲፭እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥ ፲፮ሁልጊዜ ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል። ፲፯እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤ ፲፰ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን። ፲፱ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? ፳እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።