2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና። ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው። ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና። በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። ፲-፲፪ትምክህታችን ይህ ነውና፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ እንደኖርን የሕሊናችን ምስክርነት ነው። ፲፫-፲፭በዚህም ታምኜ፥ ሁለተኛ ጸጋ ታገኙ ዘንድ አስቀድሜ ወደ እናንተ እንድመጣ፥ ፲፮በእናንተም መካከል ወደ መቄዶንያ እንዳልፍ ደግሞም ከመቄዶንያ ወደ እናንተ መጥቼ ወደ ይሁዳ በጉዞዬ እንድትረዱኝ አሰብሁ። ፲፯እንግዲህ ይህን ሳስብ ያን ጊዜ ቅሌትን አሳየሁን? ወይስ በእኔ ዘንድ አዎን አዎን አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የማስበው በዓለማዊ ልማድ ነውን? ፲፰እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም። ፲፱በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል። እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው። ፳፩በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥ ፳፪ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው። ፳፫እኔ ግን ልራራላችሁ ስል እንደ ገና ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣሁ በነፍሴ ላይ እግዚአብሔርን ምስክር እጠራለሁ። ፳፬ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፥ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና።