፩እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን? ፪ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። ፫እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው። ፬በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን። ፭ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤ ፮እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። ፯ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ ፰የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም? ፱የኵነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ፥ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና። ፲ያ የከበረ እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት በዚህ ነገር ክብሩን አጥቶአልና። ፲፩ያ ይሻር የነበረው በክብር ከሆነ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እጅግ ይልቅ በክብር ሆኖአልና። ፲፪እንግዲህ እንዲህ ያለ ተስፋ ካለን እጅግ ገልጠን እንናገራለን፥ ፲፫የዚያንም ይሻር የነበረውን መጨረሻ ትኵር ብለው የእስራኤል ልጆች እንዳይመለከቱ፥ በፊቱ መጋረጃ እንዳደረገ እንደ ሙሴ አይደለንም። ፲፬ነገር ግን አሳባቸው ደነዘዘ። ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና። ፲፭ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ጊዜ ሁሉ ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ ፲፮ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል። ፲፯ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ። ፲፰እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።