፩እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፥ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ። ፪በልባችሁ ስፍራ አስፉልን፤ ማንንም አልበደልንም፥ ማንንም አላጠፋንም፥ ማንንም አላታለልንም። ፫ለኵነኔ አልልም፤ በአንድነት ለመሞትና በአንድነት ለመኖር በልባችን እንዳላችሁ አስቀድሜ ብዬአለሁና። ፬ስለ እናንተ እምነቴ ታላቅ ነው፥ በእናንተ ምክንያት ትምክህቴ ታላቅ ነው፤ መጽናናት ሞልቶብኛል፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ከመጠን ይልቅ ይበዛል። ፭ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም፤ በውጭ ጠብ ነበረ፥ በውስጥ ፍርሃት ነበረ። ፮ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ ፯በመምጣቱም ብቻ አይደለም ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም ቅንዓታችሁን ሲናገረን በእናንተ ላይ በተጽናናበት መጽናናት ደግሞ ነው፤ ስለዚህም ከፊት ይልቅ ደስ አለን። ፰በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ አያለሁና አሁን ለንስሐ ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም፤ ፱በምንም ከእኛ የተነሣ እንዳትጎዱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና። ፲እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። ፲፩እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን እንዴት ያለ ትጋት፥ እንዴት ያለ መልስ፥ እንዴት ያለ ቁጣ፥ እንዴት ያለ ፍርሃት፥ እንዴት ያለ ናፍቆት፥ እንዴት ያለ ቅንዓት፥ እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል። ፲፪እንግዲያስ የጻፍሁላችሁ ብሆን እንኳ፥ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋታችሁ ከእናንተ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ፥ ስለ በዳዩ ወይም ስለ ተበዳዩ አልጻፍሁም። ስለዚህ ተጽናንተናል። ፲፫በመጽናናታችንም ስለ ቲቶ ደስታ አብልጦ ደስ አለን፥ መንፈሱ በሁላችሁ ዐርፎአልና፤ ፲፬ለእርሱ በምንም ስለ እናንተ የተመካሁ እንደ ሆነ አላፈርሁምና፥ ነገር ግን ሁሉን ለእናንተ በእውነት እንደ ተናገርን፥ እንደዚህ ደግሞ ትምክህታችን በቲቶ ፊት እውነት ሆነ። ፲፭ስለዚህም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደተቀበላችሁት፥ የሁላችሁን መታዘዝ እያሰበ ፍቅሩ በእናንተ ላይ እጅግ በዝቶአል። ፲፮በነገር ሁሉ ተማምኜባችኋለሁና ደስ ይለኛል።