፩ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤ ፪በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ ፫እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና። ፬ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር፥ ፭አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ እንጂ እንዳሰብን አይደለም። ፮ስለዚህም ቲቶ አስቀድሞ እንደ ጀመረ እንዲሁ ደግሞ ይህን ቸር ሥራ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ሊፈጽም ለመንን። ፯ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነትና በቃል በእውቀትም በትጋትም ሁሉ ለእኛም በፍቅራችሁ እንደ ተረፋችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ትረፉ። ፰ትእዛዝ እንደምሰጥ አልልም፥ ነገር ግን በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ፤ ፱የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ። ፲በዚህም ነገር ምክር እሰጣለሁ፤ ከአምና ጀምራችሁ ለማድረግ ብቻ ያይደለ ነገር ግን ለማሰብ ደግሞ አስቀድማችሁ የጀመራችሁት ይህ ይጠቅማችኋልና፤ ፲፩አሁንም ለማሰብ በጎ ፈቃድ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እንዳላችሁ መጠን መፈጸም ደግሞ ይሆን ዘንድ፥ ማድረጉን ደግሞ ፈጽሙ። ፲፪በጎ ፈቃድ ቢኖር፥ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም። ፲፫ለሌሎች ዕረፍት ለእናንተም መከራ እንዲሆን አይደለም፥ ትክክል እንዲሆን ነው እንጂ፤ ፲፬የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። ፲፭ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም። ፲፮ነገር ግን በቲቶ ልብ ስለ እናንተ ያንን ትጋት የሰጠ አምላክ ይመስገን፤ ፲፯ምክራችንን ተቀብሎአልና፥ ትጋት ግን ስለ በዛበት ወዶ ወደ እናንተ ይወጣል። ፲፰ከእርሱም ጋር ስለ ወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም እንልካለን፤ ፲፱ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን የጌታን የራሱን ክብርና የእኛን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በምናገለግለው በዚህ ቸር ሥራ ከእኛ ጋር እንዲጓደድ በአብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ተመረጠ። ፳ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን፤ ፳፩በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለንና። ፳፪ብዙ ጊዜም በብዙ ነገር መርምረን ትጉ እንደ ሆነ ያገኘነውን፥ አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከፊት ይልቅ እጅግ ትጉ የሚሆነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር እንልካለን። ፳፫ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር ስለ እናንተ አብሮኝ የሚሠራ ባልንጀራዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችን የሚጠይቅ ቢኖርም የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞችና የክርስቶስ ክብር ናቸው። ፳፬እንግዲህ የፍቅራችሁንና ስለ እናንተ ያለውን የትምክህታችንን መግለጫ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ለእነርሱ ግለጡ።