ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ። እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም። ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ። ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። እርሱም። ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። ፲፩በመመካቴ ሞኝ ሆኜአለሁ፤ እናንተ ግድ አላችሁኝ፤ እናንተ እኔን ልታመሰግኑ ይገባ ነበርና። እኔ ምንም ባልሆን እንኳ፥ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አልጎድልምና። ፲፪በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት በመካከላችሁ በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም በሁሉ ትዕግሥት ተደረገ። ፲፫እኔ ራሴ ካልከበድሁባችሁ ከዚህ በቀር፥ ከሌላ ቤተ ክርስቲያን ያነሳችሁበት በምን እኮ ነው? ይህን በደሌን ይቅር በሉልኝ። ፲፬እነሆ፥ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ አልከብድባችሁምም፥ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና። ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና። ፲፭እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፥ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ። ከመጠን ይልቅ ብወዳችሁ በዚህ ልክ ፍቅራችሁ የሚያንስ ነውን? ፲፮ይሁን እንጂ እኔ አልከበድሁባችሁም፤ ነገር ግን ሸንጋይ ሆኜ በተንኰል ያዝኋችሁ። ፲፯ወደ እናንተ ከላክኋቸው በአንዱ ስንኳ አታለልኋችሁን? ፲፰ቲቶን መከርሁት ከእርሱም ጋር ወንድሙን ላክሁት፤ ቲቶስ አታለላችሁን? በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? በአንድ ፍለጋስ አልተመላለስንም? ፲፱ለእናንተ ስለ ራሳችን እንድንመልስ ሁልጊዜ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ነገር ግን፥ ወዳጆች፥ እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን። ስመጣ፥ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፤ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፤ ፳፩እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ።