፩እንግዲህ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። ፪ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ። ፫እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። ፬የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። ፭ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። ፮የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል። ፯የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ። ፰በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ ፱ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። ፲ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ። ፲፩ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ ፲፪ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው፥ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤ ፲፫ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና። ፲፬ይህን አሳስባቸው፥ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፥ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። ፲፭የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። ፲፮ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤ ፲፯ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤ ፲፰እነዚህም። ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፥ ስለ እውነት ስተው፥ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ። ፲፱ሆኖም። ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፥ ደግሞም። የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል። ፳በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፥ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ ፳፩እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ፳፪ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ፳፫ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤ ፳፬-፳፮የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም።