፩በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ፪ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ፫ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። ፬እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ። ፭አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም። ፮በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። ፯መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ፰ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም። ፱በቶሎ ወደ እኔ እንድትመጣ ትጋ፤ ፲ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና፥ ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል፤ ቄርቂስም ወደ ገላትያ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤ ፲፩ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር አለ። ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው። ፲፪ቲኪቆስን ግን ወደ ኤፌሶን ላክሁት። ፲፫ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ። ፲፬የናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ እጅግ ከፋብኝ፤ ጌታ እንደ ሥራው ይመልስለታል። ፲፭አንተም ደግሞ ከእርሱ ተጠበቅ፥ የምንናገረውን እጅግ ተቃውሞአልና። ፲፮በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፥ ሁሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው፤ ፲፯ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ፥ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ። ፲፰ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ፲፱ለጵርስቅላና ለአቂላ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ። ፳ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀረ፥ ጥሮፊሞስን ግን ታሞ በሚሊጢን ተውሁት። ፳፩ከክረምት በፊት እንድትመጣ ትጋ። ኤውግሎስና ጱዴስ ሊኖስም ቅላውዲያም ወንድሞችም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ፳፪ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።