፩-፫በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ። ፬ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤ ፭-፯ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ፰ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ፱ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን? ፲እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ፲፩ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል። ፲፪ስለዚህ የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጉልበቶች አቅኑ፤ ፲፫ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፥ ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ። ፲፬ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና። ፲፭የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥ ሴሰኛም የሚሆን እንዳይገኝ፥ ፲፮ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ፲፯ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና። ፲፰ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም ወደ መለከት ድምፅም ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፤ ፲፱ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ለመኑ፤ ፳እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ ተወግሮ ይሙት የምትለውን ትእዛዝ ሊታገሡ አልቻሉምና፤ ፳፩ሙሴም። እጅግ እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤ ፳፪ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ ፳፫በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ ፳፬የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል። ፳፭ለሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ በምድር ላስረዳቸው እምቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፥ ከሰማይ ከመጣው ፈቀቅ የምንል እኛስ እንዴት እናመልጣለን? ፳፮በዚያም ጊዜ ድምፁ ምድርን አናወጠ፥ አሁን ግን። አንድ ጊዜ ደግሜ እኔ ሰማይን አናውጣለሁ እንጂ ምድርን ብቻ አይደለም ብሎ ተስፋ ሰጥቶአል። ፳፯ዳሩ ግን። አንድ ጊዜ ደግሜ የሚል ቃል፥ የማይናወጡት ጸንተው እንዲኖሩ፥ የሚናወጡት የተፈጠሩ እንደሚሆኑ ይለወጡ ዘንድ ያሳያል። ፳፰ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ ፳፱አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።