፩ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው። ፪በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። ፫ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። ፬የአይሁድ በዓልም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። ፭ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን። እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን? አለው። ፮ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ። ፯ፊልጶስ። እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት። ፰ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ። ፱አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል? አለው። ፲ኢየሱስም። ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ አለ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት። ወንዶችም ተቀመጡ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር። ፲፩ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፥ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን። ፲፪ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን። አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ አከማቹ አላቸው። ፲፫ሰለዚህ አከማቹ፥ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ። ፲፬ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ። ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው አሉ። ፲፭በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ። ፲፮በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፥ ፲፯በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር። አሁንም ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር፤ ፲፰ብርቱ ነፋስም ስለ ነፈሰ ባሕሩ ተናወጠ። ፲፱ሀያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ከቀዘፉ በኋላም፥ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ ታንኳይቱ ሲቀርብ አይተው ፈሩ። ፳እርሱ ግን። እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው። ፳፩ስለዚህ በታንኳይቱ ሊቀበሉት ወደዱ፤ ወዲያውም ታንኳይቱ ወደሚሄዱበት ምድር ደረሰች። ፳፪በነገው በባሕር ማዶ ቆመው የነበሩ ሕዝቡ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ፤ ፳፫ዳሩ ግን ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ። ፳፬ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ፥ ራሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ፳፭በባሕር ማዶም ሲያገኙት። መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ? አሉት። ፳፮ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ፳፯ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ፳፰እንግዲህ። የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት። ፳፱ኢየሱስ መልሶ። ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው። ፴እንግዲህ። እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ፴፩ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ አሉት። ፴፪ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ ፴፫የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው። ፴፬ስለዚህ። ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት። ፴፭ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም። ፴፮ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ። ፴፯አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ ፴፰ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። ፴፱ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው። ፵ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ፵፩እንግዲህ አይሁድ። ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና። ፵፪አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ። ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ። ፵፫ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። ፵፬የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ፵፭ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። ፵፮አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል። ፵፯እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። ፵፰የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። ፵፱አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ፶ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ፶፩ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። ፶፪እንግዲህ አይሁድ። ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ፶፫ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ፶፬ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ፶፭ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ፶፮ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ፶፯ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። ፶፰ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል ፶፱በቅፍርናሆም ሲያስተምር ይህን በምኵራብ አለ። ፷ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ። ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ። ፷፩ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ አላቸው። ይህ ያሰናክላችኋልን? ፷፪እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል? ፷፫ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው። ፷፬ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና። ፷፭ደግሞ። ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ። ፷፮ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም። ፷፯ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ። እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ። ፷፰ስምዖን ጴጥሮስ። ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ ፷፱እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት። ፸ኢየሱስም። እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው ብሎ መለሰላቸው። ፸፩ስለ ስምዖንም ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ተናገረ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና።