ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም፥ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፥ ቢጸጸትም ይቅር በለው። በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ በቀንም ሰባት ጊዜ። ተጸጸትሁ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው። ሐዋርያትም ጌታን። እምነት ጨምርልን አሉት። ጌታም አለ። የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ ባሪያ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ። ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ የሚለው ማን ነው? የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፥ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ የሚለው አይደለምን? ያንን ባሪያ ያዘዘውን ስላደረገ ያመሰግነዋልን? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ። የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ። ፲፩ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ፲፪ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ ፲፫እነርሱም እየጮኹ። ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ። ፲፬አይቶም። ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው። ፲፭እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ ፲፮እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ፲፯ኢየሱስም መልሶ። አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ፲፰ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ። ፲፱እርሱንም። ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ፈሪሳውያንም። የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ። የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ፳፩ደግሞም። እንኋት በዚህ ወይም። እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ፳፪ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ልታዩ የምትመኙበት ወራት ይመጣል አታዩትምም። ፳፫እነርሱም። እነሆ በዚህ፥ ወይም። እነሆ በዚያ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ አትከተሉአቸውም። ፳፬መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲህ ይሆናል። ፳፭አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል። ፳፮በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። ፳፯ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፥ የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ። ፳፰እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ፳፱ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። ፴፩በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፥ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። ፴፪የሎጥን ሚስት አስቡአት። ፴፫ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም የሚያጠፋ ሁሉ በሕይወት ይጠብቃታል። ፴፬እላችኋለሁ፥ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። ፴፭ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች ሁለተኛይቱም ትቀራለች። ፴፮ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። ፴፯መልሰውም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው? አሉት። እርሱም። ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ አላቸው።