፩ወደ ኢየሩሳሌምም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወዳሉቱ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ። ፪በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወዲያውም ወደ እርስዋ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ፫ማንም። ስለ ምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት፥ ወዲያውም ደግሞ ወደዚህ ይሰደዋል አላቸው። ፬ሄዱም ውርንጫውንም በመንገድ መተላለፊያ በደጅ ውጭ ታስሮ አገኙት፥ ፈቱትም። ፭በዚያም ከቆሙት አንዳንዶቹ። ውርንጫውን የምትፈቱት ምን ልታደርጉት ነው አሉአቸው። ፮እነርሱም ኢየሱስ እንዳዘዘ አሉአቸው፤ ተዉአቸውም። ፯ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አመጡት፥ ልብሳቸውንም በላዩ ጣሉ፥ ተቀመጠበትም። ፰ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር። ፱የሚቀድሙትም የሚከተሉትም። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ፲በጌታ ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር። ፲፩ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቅደስ ገባ፤ ዘወር ብሎም ሁሉን ከተመለከተ በኋላ፥ ጊዜው መሽቶ ስለ ነበረ ከአሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ። ፲፪በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ። ፲፫ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ፲፬መልሶም። ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ። ፲፭ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። ወደ መቅደስም ገብቶ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያወጣ ጀመር፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጭዎችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ ፲፮ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም። ፲፯አስተማራቸውም። ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። ፲፰የካህናት አለቆችም ጻፎችም ሰምተው፥ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ይገረሙ ስለ ነበር ይፈሩት ነበርና እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ፈለጉ። ፲፱ማታ ማታም ከከተማ ወደ ውጭ ይወጣ ነበር። ፳ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት። ፳፩ጴጥሮስም ትዝ ብሎት። መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው። ፳፪ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። በእግዚአብሔር እመኑ። ፳፫እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ፳፬ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። ፳፭ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። ፳፮እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። ፳፯ደግሞም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እርሱም በመቅደስ ሲመላለስ፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጥተው። ፳፰እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ወይስ እነዚህን ለማድረግ ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። ፳፱ኢየሱስም። እኔም አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም መልሱልኝ፥ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ። ፴የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ አላቸው። ፴፩እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ነው ብንል። እንግዲያውስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ፴፪ነገር ግን። ከሰው ነው እንበልን? አሉ፤ ሁሉ ዮሐንስን በእውነት እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና ሕዝቡን ፈሩ። ፴፫ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።