ወደ ቆላስይስ ሰዎች
በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ጢሞቴዎስም ወንድሙ፥ በቈላስይስ ለሚኖሩ ቅዱሳንና በክርስቶስ ለታመኑ ወንድሞች፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ይሁን። ፫-፮ይህም በዓለም ሁሉ ደግሞ እንዳለ ወደ እናንተ ደርሶአል፥ እግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ ደግሞ እንዳለ እንዲህ በዓለም ፍሬ ያፈራል ያድግማል። ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባሪያ ከሆነው ከኤጳፍራ እንዲህ ተማራችሁ፥ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው። ደግሞም በመንፈስ ስለሚሆን ስለ ፍቅራችሁ አስታወቀን። ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም። ፲-፲፪ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን። ፲፫-፲፯እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል። ፲፰እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው። ፲፱-፳፫ይህም፥ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል። ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ። ፳፬አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። ፳፭ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ። ፳፮ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። ፳፯ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። ፳፰እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው። ፳፱ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።