ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ሁሉ እንዴት ያለ ትልቅ መጋደል እንዳለኝ ልታውቁ እወዳለሁና። ልባቸው እንዲጸናና፥ በፍቅርም ተባብረው በማስተዋል ወደሚገኝበት ወደ መረዳት ባለ ጠግነት ሁሉ እንዲደርሱ የእግዚአብሔርንም ምሥጢር እርሱንም ክርስቶስን እንዲያውቁ እጋደላለሁ። የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና። ማንም በሚያባብል ቃል እንዳያስታችሁ ይህን እላለሁ። በሥጋ ምንም እንኳ ብርቅ፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና፥ ሥርዓታችሁንም በክርስቶስም ያለውን የእምነታችሁን ጽናት እያየሁ ደስ ይለኛል። እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ። ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። ፲፩የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ። ፲፪በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። ፲፫እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። ፲፬በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። ፲፭አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ፲፮እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። ፲፯እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ፲፰ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ። ፲፱እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል። ፳-፳፪እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ፳፫ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም።