ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፥ ይህ የሚገባ ነውና። ፪-፬እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው። ባሪያዎች ሆይ፥ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና። እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፥ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንዳያደላ ታውቃላችሁና። በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። ፲፩የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። ፲፪መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ፲፫ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። ፲፬-፲፮በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ ፲፯የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። ፲፰በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤ ፲፱ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ። ፳፩ነገር ግን እናንተ ደግሞ እንዴት እንዳለሁ ኑሮዬን እንድታውቁ የተወደደ ወንድምና በጌታ የታመነ አገልጋይ ቲኪቆስ ሁሉን ያስታውቃችኋል፤ ፳፪ወሬአችንን እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ወደ እናንተ የምልከው ስለዚህ ምክንያት ነው። ፳፫ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን። ፳፬ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።