ወደ ዕብራውያን
፩ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ፪ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ ፫እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ፬ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል። ፭ከመላእክትስ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም። እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ፮ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ። የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል። ፯ስለ መላእክትም። መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ፰ይላል፤ ስለ ልጁ ግን። አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። ፱ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ ፲ይላል። ደግሞ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ ፲፩እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ ፲፪እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ፲፫ይላል። ነገር ግን ከመላእክት። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ፲፬ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?