፩እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ፪ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። ፫ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። ፬አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። ፭ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤ ፮ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ፯ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኰነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። ፰አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ፱ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ ፲መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና። ፲፩ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ፲፪ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ። ፲፫እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ። ፲፬እንዲህ የሚሉት ለእነርሱ የሚሆነውን አገር እንዲፈልጉ ያመለክታሉና። ፲፭ያን የወጡበትን አገር አስበው ቢሆኑ፥ ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር፤ ፲፮አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። ፲፯-፲፱እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፥ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው። ፳ይስሐቅ ሊመጣ ስላለው ነገር ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ፳፩ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸው ባረካቸው፥ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ፳፪ዮሴፍ ወደ ሞት ቀርቦ ሳለ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፥ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ፳፫ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ፳፬ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ፳፭-፳፯የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና። ፳፰አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ። ፳፱በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ በኤርትራ ባሕር በእምነት ተሻገሩ፥ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ተዋጡ። ፴የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ። ፴፩ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙ ጋር በእምነት አልጠፋችም። ፴፪እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። ፴፫እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ ፴፬የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ፴፭ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ፴፮ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ ፴፯በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ፴፰-፵ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።