ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ። አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም። አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? ነገር ግን መጽሐፍ። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤ ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል። ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው ደግሞ። አትግደል ብሎአልና፤ ፲፩ባታመነዝርም፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግን ተላላፊ ሆነሃል። ፲፪በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ። ፲፫ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል። ፲፬ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ፲፭ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ ፲፮ከእናንተ አንዱም። በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? ፲፯እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። ፲፰ነገር ግን አንድ ሰው። አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። ፲፱እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? ፳፩አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? ፳፪እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? ፳፫መጽሐፍም። አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። ፳፬ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። ፳፭እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ፳፮ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።