፩ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና። ፪ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። ፫እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን። ፬እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ። ፭እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። ፮አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል። ፯የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤ ፰ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። ፱በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤ ፲ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም። ፲፩ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን? ፲፪ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም። ፲፫ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ፲፬ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ፲፭ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ፲፮ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ፲፯ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። ፲፰የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።