፩አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። ፪ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። ፫ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል። ፬እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል። ፭በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል። ፮ጻድቁን ኰንናችሁታል ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም። ፯እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። ፰እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና። ፱ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል። ፲ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። ፲፩እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና። ፲፪ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን። ፲፫ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር። ፲፬ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። ፲፭የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል። ፲፮እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ፲፯ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ ፲፰ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች። ፲፱ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥ ፳ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።