ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች
የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ፫-፮በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። ፱-፲፪ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። ፲፫ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥ ፲፬በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ። ፲፭አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ ፲፮እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ ፲፯እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ፲፰ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። ፲፱ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል። ፳፩ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ፳፪ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። ፳፫በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ፳፬ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። ፳፭-፳፯ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። ፳፰በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ፳፱ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።