፩ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ እኵል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ። ፪በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው። ፫ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። ፬የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ። ፭መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ። ፮ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ። ፯ፊተኛውም መልአክ ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፥ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ። ፰ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ ፱በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ። ፲ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፥ በወንዞችና በውኃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል። ፲፩የውኃውም ሲሶ መራራ ሆነ መራራም ስለተደረገ በውኃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ። ፲፪አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት። ፲፫አየሁም፥ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ። ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ።