፩ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፥ ፪የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፥ እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ፫በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ። ፬ሰባቱ ነጐድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፤ ከሰማይም። ሰባቱ ነጐድጓድ የተናገሩትን ነገር በማኅተም ዝጋው አትጻፈውም የሚል ድምፅ ሰማሁ። ፭በባሕርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አሻቅቦ ዘረጋ፥ ፮ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፥ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፥ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፥ ከዘላለምም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ። ፯ወደ ፊት አይዘገይም፥ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን፥ ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል አለ። ፰ከሰማይም የሰማሁት ድምፅ እንደ ገና ሲናገረኝና። ሂድና በባሕርና በምድር ላይ ከሚቆመው መልአክ በእጁ ያለችውን የተከፈተችውን መጽሐፍ ውሰድ ሲል ሰማሁ። ፱ወደ መልአኩም ሄጄ። ታናሺቱን መጽሐፍ ስጠኝ አልሁት። እርሱም። ውሰድና ብላት፥ ሆድህንም መራራ ታደርገዋለች በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች አለኝ። ፲ከመልአኩም እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፤ ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ። ፲፩በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ እንደ ገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል ተባለልኝ።