፩በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፥ እንዲህም ተባለልኝ። ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። ፪በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። ፫ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ። ፬እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። ፭ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። ፮እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፥ ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው። ፯ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል ያሸንፋቸውማል ይገድላቸውማል። ፰በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት። ፱ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኵል በድናቸውን ይመለከታሉ፥ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም። ፲እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስለ ሣቀዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል በደስታም ይኖራሉ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ። ፲፩ከሦስቱ ቀን ተኵልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው በእግሮቻቸውም ቆሙ፥ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው። ፲፪በሰማይም። ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ። ፲፫በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፥ ከከተማይቱም አሥረኛው እጅ ወደቀ፥ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፥ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፥ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ። ፲፬ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል። ፲፭ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም። የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል ፲፮የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ። በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ፲፯ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ። ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤ ፲፰አሕዛብም ተቈጡ፥ ቍጣህም መጣ፥ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፥ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ። ፲፱በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።