፩ በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና። ፪ እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። ፫-፭ መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው። ፮ መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን? ፯ እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ ፰ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም። ፱ ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ። ፲ በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፥ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን አላልሁም፤ ይህስ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር። ፲፩ አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ። ፲፪ በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ? በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? ፲፫ በውጭ ባሉቱ ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።