፲፩
፩ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ። ፪ ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ። ፫ ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ። ፬ ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። ፭ ራስዋን ሳትሸፍን ግን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራስዋን ታዋርዳለች፤ እንደ ተላጨች ያህል አንድ ነውና። ፮ ሴትም ራስዋን ባትሸፍን ጠጉርዋን ደግሞ ትቆረጥ፤ ለሴት ግን ጠጉርዋን መቆረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ከሆነ ራስዋን ትሸፍን። ፯ ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት። ፰ ሴት ከወንድ ናት እንጂ ወንድ ከሴት አይደለምና። ፱ ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረምና። ፲ ስለዚህ ሴት ከመላእክት የተነሣ በራስዋ ሥልጣን ሊኖራት ይገባል። ፲፩ ነገር ግን በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም። ፲፪ ሴት ከወንድ እንደ ሆነች እንዲሁ ወንድ ደግሞ በሴት ነውና፤ ሁሉም ከእግዚአብሔር ነው። ፲፫ በእናንተ በራሳችሁ መካከል ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር ልትጸልይ ይገባታልን? ፲፬-፲፮ ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም። ፲፯ ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚከፋ እንጂ ለሚሻል ስላልሆነ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ የማመሰግናችሁ አይደለም። ፲፰ በመጀመሪያ ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁና፥ በአንድ በኩልም አምናለሁ። ፲፱ በእናንተ ዘንድ የተፈተኑት እንዲገለጡ በመካከላችሁ ወገኖች ደግሞ ሊሆኑ ግድ ነውና። ፳ እንግዲህ አብራችሁ ስትሰበሰቡ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም፤ ፳፩ በመብላት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላልና፥ አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል። ፳፪ የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ማኅበር ትንቃላችሁን አንዳችም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? አላመሰግናችሁም። ፳፫ ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤ ፳፬ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም። እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። ፳፭ እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ። ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። ፳፮ ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና። ፳፯ ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ፳፰ ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ፳፱ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና። ፴ ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል። ፴፩ ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ ፴፪ ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን። ፴፫ ስለዚህ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። ፴፬ ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ። የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ።