፲፭
፩ ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ ፪ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ። ፫ እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ። መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ ፬ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ፭ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ፮ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ፯ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ፰ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ። ፱ እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤ ፲ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። ፲፩ እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ። ፲፪ ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ። ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ? ፲፫ ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ፲፬ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ ፲፭ ደግሞም። ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም። ፲፮ ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ፲፯ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። ፲፰ እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። ፲፱ በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። ፳ አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ፳፩ ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ፳፪ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። ፳፫ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤ ፳፬ በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። ፳፭ ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። ፳፮ የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ ፳፯ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን። ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። ፳፰ ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል። ፳፱ እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? ፴ እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው? ፴፩ በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ። ፴፪ እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። ፴፫ አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። ፴፬ በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። ፴፭ ነገር ግን ሰው። ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል። ፴፮ አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ ፴፯ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤ ፴፰ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል። ፴፱ ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፥ የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው፥ የእንስሳም ሥጋ ሌላ ነው፥ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፥ የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው። ፵ ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፥ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው። ፵፩ የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና። ፵፪ የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ ፵፫ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ ፵፬ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። ፵፭ እንዲሁ ደግሞ። ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ፵፮ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። ፵፯ የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። ፵፰ መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። ፵፱ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ፶ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። ፶፩-፶፫ ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ፶፬ ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ። ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ፶፭ ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? ፶፮ የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ፶፯ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ፶፰ ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።