፩-፫ ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ፬ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። ፭ እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና፤ ፮ እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም። ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ። ፯ እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው። ፰ በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፥ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደወንድሞች ተዋደዱ፥ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ፤ ፱ ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። ፲ ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ፲፩ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ ፲፪ የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው። ፲፫ በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ፲፬ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ፲፭ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። ፲፮ በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ። ፲፯ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና። ፲፰ ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ ፲፱ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ ፳ ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ፳፩ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤ ፳፪ እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።