፩ እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን? ፪ ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። ፫ እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው። ፬ በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን። ፭ ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤ ፮ እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። ፯ ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ ፰ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም? ፱ የኵነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ፥ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና። ፲ ያ የከበረ እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት በዚህ ነገር ክብሩን አጥቶአልና። ፲፩ ያ ይሻር የነበረው በክብር ከሆነ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እጅግ ይልቅ በክብር ሆኖአልና። ፲፪ እንግዲህ እንዲህ ያለ ተስፋ ካለን እጅግ ገልጠን እንናገራለን፥ ፲፫ የዚያንም ይሻር የነበረውን መጨረሻ ትኵር ብለው የእስራኤል ልጆች እንዳይመለከቱ፥ በፊቱ መጋረጃ እንዳደረገ እንደ ሙሴ አይደለንም። ፲፬ ነገር ግን አሳባቸው ደነዘዘ። ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና። ፲፭ ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ጊዜ ሁሉ ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ ፲፮ ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል። ፲፯ ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ። ፲፰ እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።